አለም አቀፉ የፕላስቲክ ብክለት ስምምነት ለምን ያስፈልጋል?
አብዛኖቻችን የፕላስቲክ ብክለት ሲባል ከምንኖርበት አካባቢ ርቀው ባሉ ውቅያኖሶችና የባህር ዳርቻዎች ብቻ የሚገኝ ችግር ሊመስለን ይችላል፡፡ ነገር ግን የፕላስቲክ ብክለትና መዘዙ ሁላችንንም በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ይነካናል፡፡ በከተማችን አዲስ አባባ በየመንገዱ የሚጣሉ ፌስታሎችና ሌሎች ፕላስቲኮች በአስፋልት ዳርቻ ያሉ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችን ይደፍናሉ እንዲሁም በየመንገዱ በቸልተኝነት የሚጣሉ ፕላስቲኮች የአካባቢያችን ፅዳት ይፈትናሉ። የፕላስቲክ ብክለት የሚያመጣው ቀውስ ግን ከዚህ እጅግ የባሰ ነው፡፡
ፌስታልና መልሰው ጥቅም ላይ የማይውሉ ፕላስቲኮች ከአገልግሎት በኋላ የሕዝብና የሀገር ችግርና ቆሻሻ ሆነው ይቀራሉ፡፡በመቶ ዓመት ዕድሜ አይበሰብሱም። ለመሬት መከላት ምክንያት ይሆናሉ። በሚያስከትሉት የአየር ብክለት ሰዎችንና የባህር አሳዎችንና እንዲሁም እንስሳትን ለበሽታዎችና ለሞት ይዳረጋሉ፡፡ የአካባቢ ብክለት በአለም አቀፍ ደረጃ ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይሰዎች ያለጊዜያቸው እንዲሞቱ ምክንያት እንደሚሆንም የአለም ባንክ ከሶስት አመታት በፊት ባወጣው ጥናት አሳውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ከሚነጨው ቆሻሻ ውስጥ 13 በመቶ የሚሆነው ፕላስቲክ ሲሆን በአንድ አመት ብቻ ወደ 80000 ቶን የፕላስቲክ
ቆሻሻ ይመነጫል ተብሎ ይገመታል፡፡ ባለፉት አመታትም የከተማዋ የነፍስ ወከፍ የፕላስቲክ ፍጆታ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ከሶስት አመት በፊት የነበረውን ቁጥር ብናይ በከተማዋ የፕላስቲክ የነፍስ ወከፍ ፍጆታ 26 ኪግ እንደደረሰ እናያለን፡፡
ምንም እንኳን በከተማዋ የፕላስቲክ ቆሻሻን እንደገና በመጠቀም፣ የቆሻሻ አስተዳደር በማዘመንና የአንድ ጊዜ የፕላስቲክ አጠቃቅምን በህግ በመግታት የፕላስቲክን አጠቃቀም ለመቀነስ እየተሞከረ ቢሆንም፣ በሀገር ደረጃ የሚደረግ ጥረት ብቻውን ግን በፕላስቲክ ምክንያት የሚመጣውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት አያስቀረውም። ለዚህም ነው ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ እየተደረገ በሚገኘው የፕላስቲከ ድርድር ውስጥ በንቃት እየታሳተፈች የምትገኘው፡፡
አገር ቤት የሚሰማ ዓለም አቅፋዊ ችግር
የፕላስቲክ ምርት ከ1950 ዓ.ም. ከነበረው 2 ሚሊዮን ቶን ዛሬ ወደ 450 ሚሊዮን ቶን በላይ አድጓል። አብዛኛው ፕላስቲክ ደግሞ ከአንድ ጊዜ ጥቅም በኃላ የሚወገድ ወይም የሚጣል ነው፡፡መልሶ ጥቅም ላይ የሚውለው ከሚመረተው አንፃር እጅግ
ትንሹ ፐርሰንት ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የፕላስቲክ ብክለት ለወንዞች፣ ለመሬት እንዲሁም ለማህበረሰብ ድንበር የሌለው ስጋት ሆኗል። በኢትዮጵያ ውስጥ የቆሻሻ አያያዝና አስተዳደር እየተሻሻለ ቢሆንም፣ ገና በበቂ መልኩ አልዘመነም ። በከተሞች መልሰው ጥቅም ላይ ሊወሉ የሚችሉ ፕላስቲኮችን በመስብስብ ላይ የተሰማሩ ሰዎች አሉ፣ ነገር ግን ከዛ አልፎ እሴት መጨመርና እንደገና ጥቅም ላይ ማዋል ላይ ያለው ስራ ዝቅተኛ ነው፡፡ ስለዚህም ቆሻሻን መሰብሰብ ብቻ ያተኮረው ስራ ብቻውን ደረጃ አመርቂ ውጤት ሊያመጣ የማይችለው፡፡
ለዚህም ነው በያዝነው ወር ኢትዮጵያን ጨምሮ የ184 ሀገራት ተወካዮች ጄኔቫ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፅህፈት ቤት በጉዳዩ ላይ የመከሩት፡፡ ምንም እንኳን መድረኩ ከዚህ በፊት እንደተረጉት ድርድሮች ያለስምምነት ቢጠናቀቅም ድርድሩ የፕላስቲክ ብክለትን ለመቀነስ የሚረዱ ትልልቅ ጉዳዮች ተነስተውበታል፡፡
አለም አቀፉ የፕላስቲክ ብክለት ስምምነት ምን ሊያመጣ ይችላል?
ስምምነቱ በርካታ ቁልፍ ጉዳዮችን ይዟል፡፡ ከፕላስቲክ ዲዛይን እስከ ቆሻሻ አወጋገድ፣ አመራረት፣ ፕላስቲክ መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል እና በታዳጊ ሀገራት የቆሻሻ አሰባሰብን በገንዘብ መደገፍ የሚሉ ቴክኒካል ጉዳዮች ይዟል፡፡ የመጀመሪያው የፕላስቲክን ምርት ሙሉ ዑደት የሚያጠቃልል ተጠያቂነትን የሚመለከት ነው፡፡ ይህ ማለት ከፕላስቲክ ምርት ጀምሮ እስከ መጠቀምና ማስወገድ ያለውን ሂደት ይመለከታል፡፡ ይህ በመጀመሪያ ፕላስቲክቶች ዲዛይን ሲደረጉም ሆነ ሲመረቱ መልሰው ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ መሆናቸውን ማረጋገጥና በካይ እንዳይሆኑ ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው የስምምነቱ አካል የአዳዲስ ፕላስቲክ ምርቶችን መቀነስ ላይና ችግር ሊፈጥሩና ሊወገዱ የሚችሉ ፕላስቲኮችን መቀነስ ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ ሌላኛው የኬሚካል ቁጥጥርን ይመለከታል፡፡ በፕላስቲክ ውስጥ የሚገኙ አደገኛ ኬሚካሎችን መጠን እንዲስተካከል በማድረግ ስምምነቱ በፕላስቲክ ምርት ላይ ጥቅም ላይ የሚውሉ ጎጂ ንጥር ነገኖችን ለመቆጣጣር የሚስችል አስራር ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ዓለም አቀፍ የዲዛይን መመዘኛዎች ማስቀመጥ የሚለው የስምምነቱ አራተኛው አካል ደግሞ ፕላስቲኮች እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያስችሉ ዲዛይኖችን ማበረታታት የሚለውን የያዘ ነው፡፡ የመጨረሻው የስምምነቱ አካል ፋይናንስ እና የእርዳታ አቅርቦት ይመለከታል፡፡ ይህም ማለት በተለይም ለታዳጊ ሀገራት የመሰረተ ልማትን ማሻሻልና የቆሻሻ ሰንሰለት ላይ የተሰማሩ አካላትን የስራ ደህንነት ማሻሻልን ይመለከታል፡፡
ለኢትዮጵያ የትኛው እርምጃ አስፈላጊ ነው?
የስምምነቱ የታችኛው ሂደት ማለትም የተሻለ የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ላይ የሚያተኩረው ኢትዮጵያን ተጠቃሚ አያደርግም፡፡ ፕላስቲክ ከተመረተና ጥቅም ላይ ከዋለ በኃላ ያሉ የማስወገድ ሂደቶች አድካሚና ውድ ናቸው፡፡ ፕላስቲክን ከአካባቢያችን በማስወገድ የተሰማራው የሰው ሀይል ልክ አሁን እንዳልው ዝቅተኛ ገቢ እያገኘና ለስራ ላይ አደጋ እየተጋለጠ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ፕላስቲኮች ከዲዛይን ጀምሮ ከፍተኛ ለውጥ ከተደረጋባቸው ማለትም በውስጣቸው ያለው አደገኛ ኬሚካል ከቀነሰና እንደገና ለመጠቀም የተዘጋጁ ከሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ስራ የተስማሩ አካላት ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ዕቃዎች ያገኛሉ፡፡ ይህም የተሻለ ገቢ እንዲያገኙና ጤናቸው የተጠበቅ አንዲሆን ያደርጋል፣ ንጹህ መሬትና ውሃም ይኖረናል።
ዓለም አቀፍ አምራቾች ለሚያቀርቡት ምርት ተጠያቂ እንዲሆኑ ከተደረጉ፣ ሰርኩላር ኢኮኖሚን ወደ ሚያበረታቱ አሰራሮችን ሊደግፉ ይችላሉ፡፡ ከአንድ ጊዜ በላይ ጥቅም የማይውሉ ምርቶችን ከማምረትም ይቆጠባሉ፡፡
ስምምነቱ ላይ ያሉ ዋና ክርክሮች—እና ኢትዮጵያ የፍላጎት
ከዚህ በፊት በተደረጉ ድርድሮች እንደታየው ሁሉ በጄኔቫ በተካሄደውም ድርድር በሀገራት መካከል ከፍተኛ ልዩነቶች ታይተዋል፡፡ አንዳንድ አገሮች እና የፕላስቲክ እና የነዳጅ ኢንዱስትሪው በፈቃድ የሚደረግ እርምጃ እና በገበያ ላይ የተመሰረተ መልሶ መጠቀም እንዲቀጥል ይፈልጋሉ ነገር ግን የፕላስቲክ ምርት ላይ የሚደረጉ ገደቦችን ይቃወማሉ። ሌሎች በተለይም ደግሞ ታዳጊ ሀገራት አገሮች፣ የአውሮፓ ህብረትና የፓስፊክና አፍሪካ አገሮች በፕላስቲክ ምርትና በኬሚካል ይዘት ላይ ገደብ የሚጥል የአለም አቀፍ ስምምነት እንዲኖር ይፈልጋሉ፡፡
የኢትዮጵያ ፍላጎት ከሁለተኛው ቡድን ጋር ነው።